#በክረምት_ወራት_ለ2ኛ_ደረጃ_ተማሪዎች_በተለያዩ_ሙያዎች_የሚሰጠው_የክህሎት_ስልጠና_መሰጠት_ተጀመረ።

Spread the love

#በክረምት_ወራት_ለ2ኛ_ደረጃ_ተማሪዎች_በተለያዩ_ሙያዎች_የሚሰጠው_የክህሎት_ስልጠና_መሰጠት_ተጀመረ።
======================
ሐምሌ 14/2018 (ወልቂጤ)፡ የወልቂጤ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽ/ቤትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሰጠው የክረምት ወራት የክህሎት ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

የስልጠና መርሃ-ግብሩ አላማ ተማሪዎች በክረምት የዕረፍት ጊዜያቸው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያሉ እውቀትና ክህሎቶችን እንዲያሳድጉ፣ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ደግሞ አቅማቸውን አውጥተው እንዲያዳብሩ፣ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁና በአጠቃላይ የቴክኒክና ሙያን ዘርፍ እንዲያውቁ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በስልጠና ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የኮሌጁ ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን እንዳሉት ታዳጊዎች የክረምት ጊዜያቸውን ሳያባክኑ በእውቀትና በክህሎት እንዲታነጹ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑንና ከዚህ በፊት በኮሌጁ የተሰጡ የክረምት ስልጠናዎች በቴክኖሎጂ ዘርፍ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ብዙ ታዋቂ ተሰጥኦዎችን ማፍራታቸው፤ ይህንንም ውጤታማ ተሞክሮ በማስቀጠል ተከታታይ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንና ይህንንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የወልቂጤ ከተማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀምዱ ካሚል በበኩላቸው ስልጠናው በልዩ ተሰጥኦና ፍላጎት ላላቸው ታዳጊዎች የተዘጋጀ ሲሆን በዚህ ክረምትም በተለያዩ ሙያዎች 327 ሰልጣኞች ስልጠናውን እንደሚወስዱ ገልፀዋል።

በመጨረሻም የስልጠናው ተሳታፊ ተማሪዎች በኮሌጁ የሚገኙ የስልጠና ወርክ ሾፓችን ተዟዙረው እንዲጎበኙ በማድረግ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *