ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉና የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ቴክኖሎጂዎችን እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡

Spread the love

ሰኔ 15/2014 ( ወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬዲዮ)

ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉና የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ቴክኖሎጂዎችን እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡

ኮሌጁ እሳት ማጥፋትን ጨምሮ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ቴክኖሎጂዎች መፍጠሩንም ገልጿል፡፡

የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር መነሻ በማድረግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ሰርቷል፤ በመስራት ላይም ይገኛል፡፡

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በርካቶች ችግሮቻቸው እንዲፈታ ከማስቻል ባለፈ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ የሚሰጧቸው መሆኑንም ይገለፃል፡፡

ታዲያ ኮሌጁ ስለ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሲያስብ ሁልጊዜ የአካባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስባል ያሉን የኮሌጁ ምክትል ዲንና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ ቦጋለ ተክሌ በዘንድሮው ዓመት በርካታ የማህበረሰቡ ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይም በተቋሙ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የሚያሰለጥኑ መምህራን እውቀት በማቀናጀት የማህበረሰቡን ችግር መነሻ ያደረገ የእሳት ማጥፊያ ቴክኖሎጂ መስራታቸውን የተናገሩት አቶ ቦጋለ ይህም በተጨባጭ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ቦጋለ ገለፃ የተለያየ አይነት የእሳት ቃጠሎ መኖሩን በመጠቆም ይህ ቴክኖሎጂ የተወሰኑ የእሳት አደጋ ቃጠሎዎችን ለማጥፋት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡

እሳትን ከማጥፋት በተጨማሪ ለችግኝ ማጠጫነት፣ የመንገድ ግንባታ በሚከናወንበት ወቅት ውሃ ለማርከፍከፍና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራው ቴክኖሎጂው ከ12 ሺ ሊትር በላይ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለውም ገልፀዋል፡፡

በአንድ ቴክኖሎጂ በርከት ያሉ ተግባራትን መከወን መቻል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዋነኛ አላማ መሆኑን ጠቁመው ይህ ቴክኖሎጂም ይህንን አላማ ያሳካ ነው ብለዋል፡፡

ብዙ ተግባራትን እንዲከውን ተደርጎ የተሰራው ቴክኖሎጂው ሀብት፣ ጊዜንና ጉልበትን ይቆጥባል ባይ ናቸው፡፡

ለዚህ አገልግሎት የተጠቀሙት መኪናም በብልሽት ምክንያት ለ14 ዓመታት በቆመበት ተነስቶ የተወሰነ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በቴክኖሎጂ ስራው ከሀያ በላይ ሙያተኞች የተሳተፉበት መሆኑንም ተገልጿል፡፡

ቴክኖሎጂው የእውቀት ሽግግር የተደረገበትና በተለይም እንደ ጉራጌ ዞን በበጋ ወቅት የቤት ቃጠሎ ስለሚበዛ ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችል ገልፀው ይህ ተሞክሮ እንዲሰፋ መደረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የወልቂጤ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን ኮሌጁ በ2014 ዓ/ም ከስልጠና ባሻገር የተለያዩ ችግር ፈቺ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና እቅዱንም ማሳካት መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

በዋናነት በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመግባባት ለትምህርትና ስልጠናው የሚያገለግሉ ግብአቶች የማምጣቱ ሂደት በማጠናከር በተለይም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

በብልሽት የቆሙ አገልግሎት የማይሰጡ የተሸከርካሪም ሆነ ሌሎች እቃዎች መልሶ በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል የሀብት ብክነትን ይከላከላል በማለት አሁን ላይ በኮሌጁ የተሰራው የእሳት ማጥፊያ ማህበረሰቡን ከማገልገል በተጨማሪ ኮሌጁንም ይጠቀምበታል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂዎች ወደ ማህበረሰቡ እንዲደርሱ አሁንም የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንዳለበት አቶ ኸይሩ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ ፦ አማን ቢካ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *