#በውጭ_ሀገራት_ሕጋዊ_የሥራ_ስምሪት_ላይ_ያተኮረ_የንቅናቄ_መድረክ_ተካሄደ።

Spread the love

#በውጭ_ሀገራት_ሕጋዊ_የሥራ_ስምሪት_ላይ_ያተኮረ_የንቅናቄ_መድረክ_ተካሄደ።
=============
ነሐሴ 20/2018 (ወልቂጤ)፡ የወልቂጤ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ፣ የወልቂጤ ከተማ ሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት እና ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤቶች በጋራ “የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት አቋራጭ መንገድ የለም!” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ የንቅናቄ መድረክ አካሂደዋል።

የኮሌጁ ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኮሌጁ ለሀገር ውስጥና ለውጭ የሥራ ገበያ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ሙያዎችን በመደበኛና በአጫጭር ጊዜ ሥልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች በቂ ሥልጠና በመውሰድና መብትና ግዴታቸውን በማወቅ ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን ብቻ እንዲከተሉ አሳስበዋል።

በመድረኩ የወልቂጤ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አምርያ ስራጅ እና የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ አቡሌ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅና የ2019 ዓ.ም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ዕቅድ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

የወልቂጤ ከተማ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ አስራት ታደለ በበኩላቸው፣ የዜጎች ደህንነት፣ ሰብዓዊ መብትና ክብር ተጠብቆ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት እንዲያገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርንና ሕገወጥ ደላሎችን መከላከል እንዲሁም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተነሱ ገንቢ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ ውይይት ተደርጎ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ በቀጣይም በየክ/ከተማው የንቅናቄ መድረኩን በትኩረት እንዲካሄድ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩ የከተማና የቀበሌ አመራሮች፣ የወጣትና የሴቶች ተወካዮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *